መተዳደሪያ ደንብ

መግቢያ

በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) እና በአጋር ድርጅቶች አመራር በአገራችን ያስመዘገብናቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦችን አስጠብቆ ለማስፋት፣ ስህተቶችን ለማረም እና የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የድርጅታችንን ቅርጽና ይዘት ወቅቱ ለሚጠይቀው ትግል በሚመጥን መልኩ መቀየር በማስፈለጉ፤ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች ሀገር በመራንባቸው ዓመታት በአመዛኙ ተመሳሳይ የፖለቲካ ዓላማ፣ ፕሮግራም እና መሰረታዊ አቅጣጫ እየገነባን የመጣን በመሆኑ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል እና ስህተቶችን በማረም ወደ ሚቀጥለው የትግል ምዕራፍ ለመሸጋገር አስቻይ አቅም ያለን በመሆኑ፤ የምናካሂደው ውህደት እያንዳንዱ ድርጅት የነበረውን የአላማና የተግባር ውህደት በአዲስ መንፈስ ይበልጥ በማጠናከር የተሻለ ኃይል እንድናሰባስብ የሚያስችለን በመሆኑ፤ በኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔዎች የፓርቲ ውህደት አጀንዳ በተከታታይ ቢነሳም ሳይወሰንና ሳይፈፀም መቆየቱን ግምት ውስጥ በማስገባት 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የዝግጅት ስራዎች በፍጥነት ተጠናቀው ድርጅቶቹ ወደ ውህደት እንዲሸጋገሩ ያስቀመጠውን አቅጣጫ መፈፀም በማስፈለጉ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እና የተለያዩ ማንነቶች በጋራ ባካበቱት እሴት የተገነባችና የጋራ ራዕይ ያላቸው ህዝቦች መኖሪያ ህብረ ብሄራዊት ሀገር መሆኗን በመገንዘብ፣ የሃገራችን ኢትዮጵያን እድገትና የጋራ ብልፅግና እውን ለማድረግ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ፣ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ ስርዓት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት፣

ቀጣይነት ያለው ብልፅግናን የሚያረጋግጥ ሁለንተናዊ ማህበራዊ ልማትና ሀገራዊ ክብርን ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት፣ አገራችንን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለማሻገር አዲስ ራእይና አዲስ ትርክት እንደሚያስፈልግ በማመን፣ የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት፤ የግለሰብና ቡድን መብቶች በሚዛኑ የሚከበሩባት፤ የበለፀገች፣ ሕብረ-ብሔራዊ ማንነቷ የዳበረና አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ባለን ቁርጠኝነት፣ ይህንንም ለመተግበር በመደመር አስተሳሰብና በአንድነት ቅኝት በመነሳት፣ ልናያት የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመገንባት የእያንዳንዳችንን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት የበኩላችንን ሚና ለመጫወት በከፍተኛ ቆራጥነት ተሰባስበን መታገል በማስፈለጉ፣ የብልፅግና ፓርቲ (ብልፅግና) የሚመራበት የመተዳደሪያ ደንብ መቅረጽ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ይህ መተዳደሪያ ደንብ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተደነገጉትን ህጎች የሚያከብር የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ (ብልፅግና) ሰነድን በመስራች ጉባዔያችን መክረንበት ህጋዊ የፓርቲው ሰነድ አድርገን አጽድቀናል።

ምዕራፍ አንድ

ጠቅላላ ድንጋጌዎች

አንቀጽ 1. ርዕስ ይህ መተዳደሪያ ደንብ “በብልፅግና ፓርቲ መሥራች ጉባኤ የጸደቀ የብልፅግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።

አንቀጽ 2. የፓርቲው መጠሪያ የፓርቲው መጠሪያ “የብልፅግና ፓርቲ” በእንግሊዘኛ Prosperity Party ነው።

አንቀጽ 3. የፓርቲው አርማ

አንቀጽ 4. የአርማው ትርጉም አርማው የሀገራችንን ህብረ ብሄራዊነትን፣ ሀገራዊ አንድነትንና ብሄራዊ ኩራትን፤ ሰላምን፤ ዴሞክራሲንና የብልፅግና አስተሳሰብ የያዘ ሆኖ ከውስጥ ወደ ውጭ እየሰፋ የሚሄድ የቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስሮችን የሚያመላክት ይሆናል። 

አንቀፅ 5. የፓርቲው የስራ ቋንቋ/ዎች ሀ. ፓርቲው ለሁሉም የአገራችን ቋንቋዎች ሙሉ እውቅና ይሰጣል፤ ለ. የፓርቲው የስራ ቋንቋ ክልሎች በህገ መንግስታቸው የስራ ቋንቋ ይሆናሉ ብለው ያጸደቋቸው ቋንቋዎች ይሆናሉ። ሐ. ክልሎችና የአካባቢ ቅርንጫፍ ፓርቲ ፅ/ቤቶች የየራሳቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ቢያንስ አንድ የፓርቲውን የስራ ቋንቋ በተጨማሪነት መጠቀም አለባቸው። 

አንቀጽ 6. የፓርቲው ልሳን 

1) የፓርቲው ልሳን “ብልፅግና” ነው። 

2) የፓርቲው ልሳን በፓርቲ የስራ ቋንቋዎች የሚዘጋጅ ብዝሃ ልሳን ነው። 

3) የዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (2) እንደተጠበቀ ሆኖ በሌሎች ተጨማሪ ሀገራዊና የውጭ ቋንቋዎች ሊዘጋጅ ይችላል። 

አንቀጽ 7. የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት እና ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች 

1) የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ይሆናል፤ 

2) የፓርቲው ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች በየክልሎች ዋና ከተማዎች እና ለፌዴራል መንግስት ተጠሪ በሆኑ ከተማ አስተዳደሮች ይሆናሉ፤ 

3) የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ (2) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ፓርቲው በዞን፤ በወረዳና በቀበሌ እንዲሁም እንደአስፈላጊነት ኢትዮጵያውን በብዛት ባሉባቸው ውጭ አገራት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሊያቋቁም ይችላል። 

አንቀፅ 8. የፓርቲው የአደረጃጀትና አሰራር መርሆዎች 

1) ዓላማ የብልፅግና ፓርቲ አላማ ጠንካራ፣ ዴሞክራሲያዊና ቅቡልነት ያለው ዘላቂ ሀገረመንግስት እና ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ