ኢትዮጵያዊ ስነምግባርና የኢትዮጵያዊነት ስነልቦና ፈፅሞ ከሌላቸው እኩይ ቡድኖች በንጹሃን ላይ የሚፈጸመው ማናቸውም ጥቃት ሊቆም ይገባል፡፡

 ኢትዮጵያዊነትን የሚያራክስ፤ የኖርንበትንና የሚገልጸንን ማንነት የሚያጠለሽ እኩይ ተግባር ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተሰባጥረው በአንድ የሚኖሩባት፣ ስለአገራቸው አንድነት አንድ ነብሳቸውን ሳይሰስቱ የሚሰጡባት የአብሮነት ተምሳሌት አገር ነች፡፡ ዛሬ ይህ ትልቁ መገለጫችን እንዲጠፋ በማድረግ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ንጹሃን የሚገደሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
መተማመን ጠፍቶ ተምሳሌት የሆነችው አገራችን ህልውናዋ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ለዓመታት የሚቻለውን ሁሉ ሲያሴራና ውንብድና ሲፈጽም የኖረው ህወሓት ዳግም ላይመለስ አክርካሪው የተመታ ቢሆንም ርዝራዦቹ ዛሬም በንጹሃን ደም መቆመራቸውን ቀጥለዋል፡፡ የዚህ ተሸናፊ ቡድን እሳቤ ተሸካሚም ሆነ ለእኩይ ዓላማ በዚህ መንገድ ላይ የተሰማራ ማንኛውም ኃይል የህወሓት እጣ ፈንታ የሚደርሰው መሆኑ የማያወላዳ ሃቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መዳፈር መጨረሻው ውድቀት ነው፡፡
ስለንጹሃንና ስለአገር አንድነት ሲባል ኢትዮጵያዊነት ስነምግባር በሌለው አኳኋን እኩይ ተግባር ላይ የተሰማራን ማንኛውም ኃይል የአገራችን ቡሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ መቆማቸውንና መፋለማቸውን መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ መንግስትም ሆነ ህዝብ ከዚህ በኋላ ከኢትዮጵያዊነት ስነምግባር ያፈነገጡ ተግባራትን የሚፈጽሙ ቡድኖችን መሸከም የሚችል ጫንቃ የላቸውም፡፡